In NewsJune 27, 20231 Minutes

ሚኒስቴሩ ከዓለማቀፉ ሃይፈር ፕሮጀክት ኢንተርናሽናል ጋር በጥምረት ለመስራት ስምምነት ተፈራረመ

በዛሬው ዕለት በመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር በተከናወነው ስነ-ስርዓት ላይ ስምምነቱን የተፈራራሙት ክብርት ሚኒስትር ኢ/ር አይሻ መሃመድና የሃይፈር ፕሮጀክት ኢንተርናሽናል ፕሬዚዳንትና ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሶሪታ ሳንዶሻ ናቸው፡፡
በዚሁ ስነ-ስርዓት ላይ ክብርት ሚኒስትሯ እንደተናገሩት ኢትዮጵያ የአየር ንብረትን መሰረት ያደረጉ ዘላቂ የልማት ተግባራትን ለመተግበር በምታደርገው ጥረት ከሃይፈር ፕሮጀክት ኢንተርናሽናል ጋር የተደረገው የትብብር ስምምነት ትልቅ አቅምን የሚፈጥር ነው፡፡
ስምምነቱ በተለይም የቆላማና አርብቶ አደር የልማት ስትራቴጂ በመንደፍ፣ በአነስተኛ አርሶአደሮች ደረጃ የእንስሳትና ተዋፅኦ ሃብቶችን ገበያ መር ከማድረግና የገበያ ሰንሰለቶችም ውጤታማ በሆነ መልኩ ከመዘርጋት አኳያ ትልቅ ሚና እንደሚኖረውና በግሉ ሴክተር የሚመራ አዋጭ የመስኖ ፕሮግራሞችን ለመተግበር ትልቅ ሚና ይኖረዋል፡፡
የሃይፈር ፕሮጀክት ኢንተርናሽናል ፕሬዚዳንትና ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሶሪታ ሳንዶሻ በበኩላቸው ከሚኒስቴሩ ጋር በትብብር በመስራታቸው መደሰታቸውን ገልፀው ሃይፈር ፕሮጀክት ኢንተርናሽናል ለአርሶ አደሮች ተደራሽና ዘላቂ የገበያ ትስስሮችን ለመዘርጋት ባለው ዓላማ መሰረት ሚኒስቴሩ በሚያከናውናቸው ተግባራት በዘላቂነት አብሮ ለመስራት ቁርጠኛ መሆናችንን እናረጋግጣለን ብለዋል፡፡
ሃይፈር ፕሮጀክት ኢንተርናሽናል ለትርፍ ያልተቋቋመና ከአነስተኛ አርሶ አደሮች ጋር በተያያዘ ረሃብንና ድህነትን በዘላቂነት ለማስወገድ የሚሰራ ተቋም ነው፡፡