In NewsApril 12, 20232 Minutes

የጨልጨል መስኖ ልማት ፕሮጀክት በ5.15 ቢሊዮን ብር ግንባታው እየተከናወነ ነው ፡፡

በመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር ባለቤትነት የጨልጨል መስኖ ልማት ፕሮጀክት በ5.15 ቢሊዮን ብር ግንባታው በኦሮሚያ ክልል በምስራቅ ባሌ ዞን በራይቱና ጊኒር ወረዳዎች እየተከናወነ ይገኛል፡፡ ይህ ፕሮጀክት ሙሉ ለሙሉ ሲጠናቀቅ 4146 ሄክታር በማልማት ከ9000 በላይ አርብቶአደሮችና ከፊል-አርብቶአደሮችን ተጠቃሚ ያደርጋል፡፡

የጨልጨል ግድብ ግንባታ ፕሮጀክት የሚገነባው በራይቱና ጊኒር ወረዳዎች አዋሳኝ ቦታ የዌብ ወንዝ ገባር በሆነው በጨልጨል ወንዝ ላይ ሲሆን የመስኖ ልማት አውታሮች ደግሞ በራይቱ ወረዳ ውስጥ ነው ፡፡
የጨልጨል ግድብ ከፍታው 46.5 ሜትር፣ ርዝመቱ 681 ሜትር ሲሆን ግደቡ 50 ሚሊዮን ሜትር ኩብ ውሃ በመያዝ 341.8 ሄክታር ቦታ በውሃ ይሸፈናል ፡፡ እንደዚሁም እስከ 1.5 ኪሎ ሜትር ወደ ኋላ ውሃው ይተኛል፡፡

ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ በራይቱ ወረዳ በዓመት ውስጥ የተለያዩ ሰብሎችን በቆሎ ፣ ስንዴ፣ ማሽላ ፣ፓፓያ ፣ሙዝ ፣ሽንኩርትና ቲማቲም የመሳሰሉትን ከ 2—3 ጊዜ ማምረት ያስችላል ፡፡

የግድብና የመስኖ ልማቱ ግንባታ በዋናነት የሚያካትተው 47.5 ኪሎ ሜትር ዋና ቦይ ሲሆን 3.5 ኪሎ ሜትር ከተገነባ በኃላ በግራ 21.5 ኪሎ ሜትር እና 22.6 ኪሎ ሜትር በቀኝ የሚገነባ ይሆናል ፡፡ በተጨማም 35.2 ኪሎ ሜትር ሁለተኛ ቦይና 168 ኪሎ ሜትር 3ኛ ቦይ ይገነባል ፡፡

ፕሮጀክቱ በሁለት ሎት ተከፍሎ የሚሰራ ሲሆን ሎት አንድ የግድብ ግንባታና ተያያዥ ስራዎችን ግንባታን ሲያከናውን የነበረው የመጀመሪያው ስራ ተቋራጭ ድርጅት ስራውን ከአቋረጠ በኃለ አለማየው ከተማ ጠቅላላ ስራ ተቋራጭ ድርጅት ስራውን ለመስራት የኮንትራት ውል ገብተዋል፡፡ ይህ ስራ ተቋራጭ ድርጅት ስራውን ለመጀመር የማሽነሪና የሰው ሃይል ሞቢላይዜሽን ጀምረዋል፡፡ እንዲሁም ሎት ሁለትን የመስኖ መሬት ዝግጅት፣ ዋና ካናልና ተያያዥ ስራዎችን ግንባታውንም እያከናወነ ያለው የኦሮሚያ ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን ነው ፡፡ ይህ ድርጅት ከአሁን በፊት ኮንትራቱ ለሁለት ጊዜ የተራዘመለት ሲሆን በቶሎ አስፈላጊውን ማሽነሪ አስገብቶ ማይሰራ ከሆነ ፕሮጀክቱ በተያዘለት ጊዜ ማጠናቀቁ አዳጋች ሊሆን ይችላል፡፡

የፕሮጀክቱ ግንባታ በ2015 በጀት ዓመት መጋቢት ወር መጨረሻ ድረስ የሎት አንድ 13.68 % እንዲሁም ሎት ሁለት 74.75% ደርሰዋል፡፡

በፕሮጀክቱ ወንድ 430 ሴት 79 በጠቅላላው 509 ዜጎች ጊዝያዊና ቋሚ የሥራ እድል አግኝተዋል፡፡
የፕሮጀክቱ ተግዳሮቶች የንዑስ ተቋራጭ ድክመት ፣የጉልበት ሰራተኛ እጥረት እና የማሽን ዕጥረት ሲሆኑ ችግሩን መፍታት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ተደርገዋል ፡፡

ፕሮጀክቱ በታህሳስ 2012 የተጀመረ ሲሆን በ2018 በጀት ዓመት መጨረሻ ለማጠናቀቅ ታቅዶ እየተሰራ ነው፡፡